የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን አዲስ ግጭት የሚመለከት “አስቸኳይ ስብሰባ” እንዲጠራ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ 

በኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው “አዲስ ግጭት እየተስፋፋ በመሆኑ” የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን የሚመለከት “አስቸኳይ ስብሰባ” ሊጠራ እንደሚገባ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ። የህብረቱ የሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ መወያያ ለማድረግ “የጅምላ ጭፍጨፋ እስኪከሰት ወይም የሲቪል ሰዎች ግድያ በከፍተኛ መጠን እስኪጨምር መጠበቅ እንደማይኖርበት” የድርጅቱ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ አሳስበዋል።

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈረመው እና “አሁን በተግባር የፈረሰው” ግጭት የማቆም ስምምነት ዋና አደራዳሪ የነበረው የአፍሪካ ህብረት፤ ካለፈው ስህተቱ ተምሮ ምላሽ የሚሰጥባቸውን ስርዓቶች ስራ በማስጀመር “እጅግ ከመርፈዱ በፊት አባል ሀገራቱን ማስተባበር እንደሚኖርበት” ኃላፊው ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ከፍተኛ ስጋት የተጫነውን ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው፤ ዛሬ አርብ መስከረም 22፤ 2019 ባወጣው መግለጫ ነው። 

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚሁ መግለጫው፤ በትግራይ፣ በአማራ እና አፋር ክልሎች እየተደረገ በሚገኘው ውጊያ “በከባድ መሳሪያ ድብደባዎች እና የአየር ጥቃቶች የሰላማዊ ሰዎች ንብረት መውደሙን” የሚጠቁሙ ተአማኒ ሪፖርቶች መቀበሉን አስታውቋል። የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ከተቀበላቸው ሪፖርቶች ውስጥ “የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ተጠናክሮ መቀጠሉን፤ ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህጎች እና የሰብአዊ መብት ህጎች ሊጥሱ የሚችሉ ድርጊቶች” መፈጸማቸውን የሚጠቁሙ እንደሚገኝበት በመግለጫው አስፍሯል።

የአማራ ፋኖን ጨምሮ የትግራይ ኃይሎች እና አጋሮቻቸው በአንድ በኩል፤ መከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቹ በተቃራኒው ሆነው የሚያደርጉት ውጊያ መስከረም 12፤ 2019 ከተቀሰቀሰ በኋላ፤ በደቡባዊ ትግራይ፣ ሰሜናዊ አማራ እና ምዕራባዊ አፋር መጠናከሩን አምነስቲ ጠቁሟል። ድርጅቱ በውጊያው “በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል” ካለው ከባድ መሳሪያ በተጨማሪ አክሱም እና መቐለ ከተማን ጨምሮ በመላው ትግራይ ክልል ከአየር የሚፈጸሙ ጥቃቶች መጠናከራቸውን አስታውቋል። 

በእነዚህ የአየር ጥቃቶች በርካታ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሲቪል መሰረተ ልማቶች መውደማቸውን ወይም ዒላማ መደረጋቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች በእጅጉ እንዳሳሰቡት አምነስቲ በመግለጫው አስፍሯል። ከባድ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ የዋሉባቸው፤ በማይጨው፣ በአላማጣ ከተሞች እና በዙሪያቸው በተደረጉ ውጊያዎች፤  ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት መደረጉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በመግለጫው አስፍሯል። 

በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙት ሁለቱ ከተሞች የተደረጉ ውጊያዎች ወሳኝ መሰረተ ልማቶችን ለአደጋ ማጋለጣቸውንም ጠቁሟል። ትግራይን ጨምሮ በሶስት ክልሎች እየተደረገ የሚገኘው ውጊያ “ወደ ቀጠናው ሊስፋፋ ይችላል” የሚለው ፍርሀት እየጨመረ እንደሚገኝ የጠቀሱት የአምነስቲ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር፤ የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን የሚመለከት “አስቸኳይ ስብሰባ” መጥራት እንዳለበት አሳስበዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ የአገልግሎቱ መቋረጥ “መንግስት በሲቪክ ምህዳሩ ላይ አድርጎታል” ካለው ገደብ ጋር ተዳምሮ፤ በገለልተኛ ወገኖች ከሚደረግ ክትትል ውጪ “አስከፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እየተፈጸሙ ሊሆን ይችላል” የሚል ስጋት አለው። ቲገረ ቻጉታህ በኢትዮጵያ የትጥቅ ግጭት ሲደረግ፤ በግጭት በተጠቁ አካባቢዎች የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶችን ማቋረጥ “በደንብ የተለመደ” ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል።

ኃላፊው መሰል ገደቦች በግጭቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ግፎችን መደበቃቸውን እና ሰላማዊ ሰዎችን ከተቀረው ዓለም መነጠላቸውን አስታውሰው፤ የሚመለከታቸው አካላት የተቋረጡ የቴሌሚዩኒኬሽን አገልግሎቶችን “በአስቸኳይ እንዲያስጀምሩ” ጥሪ አቅርበዋል። እነዚሁ አካላት “በዚህ ወሳኝ ወቅት”፤ ሰላማዊ ሰዎችን ሕይወታቸውን ሊታደግ ከሚችል “መረጃ እና እገዛ አለመቆራረጣቸውን” ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በመግለጫው በሰሜን ኢትዮጵያ አዲስ ውጊያ የተቀሰቀሰው፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተደጋጋሚ የትጥቅ ግጭቶች እየተካሄዱ በሚገኝበት ወቅት እንደሆነ  አስታውሷል። እነዚህ የትጥቅ ግጭቶች በመላ አገሪቱ የሚገኙ ማህበረሰቦችን “ማውደማቸውን” የጠቀሰው አምነስቲ፤ በውጊያዎቹ የሚሳተፉ አብዛኞቹ የታጠቁ ቡድኖች በብርቱ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ህግ ጥሰቶች እንደሚወነጀሉ ጠቁሟል።

ይሁንና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ እንደሚለው፤ “የጥሰቶቹ ስፋት እና ክብደት ከፍተኛ ቢሆንም ትርጉም ያለው እና ገለልተኛ ተጠያቂነት አሁንም በአብዛኛው አልታየም።” ቲገረ ቻጉታህ “ስር የሰደደ” ላሉት ለዚህ የተጠያቂነት መጥፋት፤ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፍ ተዋናዮች መፍትሔ መፈለግ እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ኃላፊው ሰላማዊ ሰዎችን ከጉዳት ለመጠበቅ፤ በኢትዮጵያ በግጭት የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች፣ የተፈጸሙ ጥሰቶች በገለልተኝነት እንዲመረመሩ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክተዋል። ይህንን ለማስቻልም “አፋጣኝ እርምጃ” መውሰድ እንዳለባቸውም ዳይሬክተሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። እርምጃው ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ ድርጅቶች እና የሰብአዊ መብቶች ተከታታዮች፤ ስራቸውን ያለ ገደብ እንዲያከናውኑ የሚያስችል መሆን እንዳለበት አምነስቲ አስገንዝቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]