ላለፉት 10 ቀናት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ተቋርጦ የነበረው የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በድጋሚ መጀመሩን የከተማይቱ አራት ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። አገልግሎቱ ወደ ነበረበት የተመለሰው ዛሬ እሁድ መስከረም 24፤ 2019 ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ተኩል ገደማ እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።
በአብዛኛው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መንግስታዊው ኢትዮ ቴሌኮም ይሰጣቸው የነበሩት የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎቶች የተቋረጡት ሐሙስ መስከረም 14 ምሽት ላይ ነበር። ሌላኛው የቴሌኮም አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅት የሆነው የሳፋሪኮም ኔትወርክ ግን እስከ አርብ እኩለ ቀን ድረስ ሲሰራ ቆይቶ ተቋርጧል።
የኢትዮ ቴሌኮም እና የሳፋሪኮም የኢንተርኔት እና የስልክ “ኔትወርኮቻቸውን እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ” የሰጠው፤ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መሆኑን የዲፕሎማቲክ ምንጭን ጨምሮ ስለጉዳዩ የሚያውቁ አራት ግለሰቦች እንደነገሩት “ሮይተርስ” በወቅቱ ዘግቦ ነበር። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዛሬ እሁድ ያነጋገረቻቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፤ በቀጥታ ስልክ መደወል እንደቻሉ የኢንተርኔት አገልግሎትም እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንተርኔት አገልግሎት በከተማይቱ በድጋሚ መጀመሩን ተከትሎ በሞባይል ስልክ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮችም ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በዚህም መሰረት የከተማይቱ ነዋሪዎች የኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት የሆነውን “ቴሌ ብር”ን ጨምሮ የባንኮች ተመሳሳይ መተግበሪያዎችን መጠቀም መጀመራቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም በከተማይቱ በርካታ ደንበኞች እና ቅርንጫፎች ያሉት መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ግን አሁንም አገልግሎት እንደማይሰጥ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። በትግራይ ክልል ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በነበረው የጥሬ ገንዘብ እጥረት ምክንያት የክልሉ ነዋሪዎች መሰረታዊ ሸቀጦችን ለመሸመት እና አገልግሎት ለማግኘት የሚጠቀሙት የሞባይል የገንዘብ ዝውውርን ነው።
በበርካታ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ በሞባይል ገንዘብ ለማስተላለፍ ተመራጭ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎት ነው። በትግራይ ክልል የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ፤ በክልሉ የባንክ ሂሳብ ያወጡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች “አካውንታቸውን” መጠቀምም ሆነ በሞባይል ገንዘብ ማስተላለፍ እንዳልቻሉ ባለፉት ቀናት ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ ነበር።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ማብራሪያ ባይሰጥም፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ደንበኞቹ ወደ ተወሰኑ ቅርንጫፎቹ በመሄድ አገልግሎት መስጠት ያቋረጡ የባንክ ሂሳቦች “ማስለቀቅ” እንደሚችሉ አስታውቆ ነበር። ይህንን የሰሙ በርካታ የባንኩ ደንበኞች፤ ወደ እነዚህ ቅርንጫፎች በመሄድ አገልግሎቱን ለማግኘት በረዣዥም ሰልፎች ሲጠብቁ ከቀናት በፊት ታይተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

































