በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ አገራት ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት እና የግዛት አንድነት መከበር እንዳለበት የቡድን ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሳሰቡ

የአፍሪካ ቀንድ የጸጥታ ሁኔታ በተለይም “ቀጠናዊ ግጭት” ሊቀሰቀስ የሚችለው የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ድንበር ተሻጋሪ ውጥረት እንዳሳሰባቸው በኢኮኖሚ የበለጸጉት የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስጋታቸውን ገለጹ። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ ማስጠንቀቂያውን የሰጡት በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ከተካሄደ ስብሰባ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው።

በፓሪስ የተካሄደው ስብሰባ የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፖን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት ነው። ይህንኑ ስብሰባ፤ ከሰባቱ ሀገራት ከፍተኛ ዲፕሎማቶች በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይም ታድመውበታል። 

በስብሰባው መጨረሻ ይፋ በተደረገው መግለጫ፤ የኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ቀውሶች ላይ ሀገራቱ ያላቸውን አቋም ያንጸባረቀ ሲሆን ግጭት ውስጥ የሚገኙት የሱዳን፤ የዩክሬን እና የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ተካተዋል። የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተው የመግለጫው ክፍል፤ ሀገሪቱ ከኤርትራ ጋር የገባችበት ውጥረት ተነስቷል።   

የቡድን ሰባት ሀገራት በመግለጫቸው፤ “ሁሉም ወገኖች” ውጥረቱን የሚያባብሱ እርምጃዎች ከመውሰድ እንዲቆጠቡ እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ ጥሪ አቅርበዋል። ሰብአዊ እርዳታ ደህንነቱ ተጠብቆ ያለ ገደብ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲደርስ፣ ሲቪል ሰዎች በተለይም ሴቶች እና ህጻናት ከጥቃት እንዲጠበቁም ሀገራቱ አሳስበዋል።

የቡድን ሰባት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያሉ ሁሉም ሀገራት “ሉዓላዊነት፣ ፖለቲካዊ ነጻነት እና የግዛት አንድነት መከበር” እንዳለበት በመግለጫቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። ሀገራቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአፍሪካ ህብረት ውጥረቱን ለማርገብ እና ድርድር ለማመቻቸት ለሚያደርጉት ጥረት ድጋፋቸውን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

We are hiring!