በጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ “ለመጨረሻ ጊዜ” አምስት የምርመራ ቀናት ተፈቀደ

በሃሚድ አወል

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ “በሽብር ፈጠራ ወንጀል” በተጠረጠሩት ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ እና ጎበዜ ሲሳይ ላይ ለሁለተኛ ጊዜ አምስት የምርመራ ቀናት ፈቀደ። ፍርድ ቤቱ የምርመራ ቀናቱን የፈቀደው ለመጨረሻ ጊዜ መሆኑን ዛሬ አርብ መስከረም 6፤ 2015 በዋለው ችሎት አስታውቋል።

የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው፤ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ በተፈቀዱለት ሰባት የምርመራ ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራት ለማድመጥ ነበር። ፖሊስ በተፈቀዱለት ቀናት ተጠርጣሪዎችን ማነጋገሩን እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃዎች መጠየቁን አስረድቷል። 

ከዚህ በተጨማሪም  የተጠርጣሪዎችን የጣት አሻራ መውሰዱን እና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ለምርመራ መላኩን ለችሎቱ ገልጿል። ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 ጀምሮ ሁለቱን የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አስሮ እየመረመረ የሚገኘው የፌደራል ፖሊስ “ቀሪ ስራዎችን ለማከናወን” በሚል 14 የምርመራ ቀናት እንዲፈቀዱለት የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ጠይቋል።

ፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ከጠየቀባቸው ምክንያቶች መካከል “በወንጀል አብረው የተሳተፉ ግብረ አበሮቹን ተከታትሎ ለመያዝ” የሚለው ይገኝበታል። ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከግል እና ከመንግስት ባንኮች እንዲሁም “ከሚመለከተው አካል” የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ ውጤት ማምጣት የሚሉት በፖሊስ በተጨማሪ ምክንያትነት ቀርበዋል። 

ሁለቱን ጋዜጠኞች ወክለው በችሎት የተገኙት አራት ጠበቆች ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የተጠርጣሪዎችን ዋስትና እንዲያስጠብቅ ጠይቀዋል። ከጠበቆቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ አልጋው፤ ፖሊስ የጠቀሳቸው ማስረጃዎች “ተቋማት ለተቋማት የሚያደርጉት የመረጃ ልውውጥ ስለሆነ የተጠርጣሪዎችን በእስር መቆየት አያስፈልግም” ሲሉ የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

“ፍርድ ቤቱ በቂ ነው ብሎ ያመነበትን ሰባት ቀን ሰጥቷል” ያሉት አቶ አዲሱ፤ “እስካሁን ምንም አይነት ምስክር አለመስማቱ ፖሊስ ስራውን በትጋት እየሰራ አለመሆኑን ያሳያል” ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። የደንበኞቻቸው በዋስትና መውጣት ፖሊስን የምስክር ቃል ከመቀበል እንደማያግደውም አክለዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁ በበኩላቸው “ሁለቱ ጋዜጠኞች የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት ሚዲያን ተጠቅመው ነው። ስለዚህ የሰው ምስክር አያስፈልግም” ሲሉ ተከራክረዋል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዎች በዋስትና ቢወጡ “ከሽብር ቡድኑ ጋር በመቀላቀል ሌላ ተጨማሪ ወንጀል ሊፈጽሙ ይችላሉ” እንዲሁም “በተፈለጉበት ጊዜ ዋስትናውን አክብረው ሊቀርቡ አይችሉም” የሚሉ “ጥርጣሬዎች” እንዳሉት በማንሳት የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል። የፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኞቹን የጠረጠራቸው፤ አዲስ አበባ ሆነው “በማህበራዊ ሚዲያ ወንጀል ፈጽመዋል” ብሎ አለመሆኑንም ለችሎቱ ገልጿል።

 “እነዚህ ሰዎች ጦር ግንባር የነበሩ ናቸው” ያለው መርማሪ ፖሊስ፤ “እነሱ ላይ የሚመሰክሩ የሰው ምስክሮች አሉን” ሲል ለችሎቱ አስረድቷል። ነገር ግን ፖሊስ “አሉኝ” ያላቸው ምስክሮች የሚገኙት “የደህንነት ስጋት ያለበት ቀጠና” ባለበት የአማራ ክልል መሆኑን በመጥቀስ፤ ቃል ለመቀበል መቸገሩን ገልጿል።

ከምስክሮች መገኛ ቦታ ጋር በተያያዘ ከተጠርጣሪዎች ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ “ምስክሮች ያሉበት አካባቢ የደህንነት ስጋት መቼ እንደሚፈታ አይታወቅም። ላልታወቀ ጊዜ ቀጠሮ ሊፈቀድ አይገባም” ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል። “ፖሊስ በደህንነት ስጋት መሄድ በማይችልበት ቦታ፤ ተጠርጣሪዎች ሄደው ምስክሮችን ያስፈራራሉ ተብሎ አይታሰብም” ሲሉም ጠበቃው የደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲከበር ችሎቱን ጠይቀዋል። 

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ፖሊስ ከመንግስት እና ከግል ተቋማት “አመጣለሁ” ያላቸው ማስረጃዎች “ከጊዜ ቀጠሮ ጋር የሚገናኝ ባለመሆኑ” እንደማይቀበለው አስታውቋል። ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ከምስክሮች ቃል መቀበል ጋር በተያያዘ “ለመጨረሻ ጊዜ አጭር ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊ ነው ብሎ ስላመነ” አምስት የምርመራ ቀናትን ለፖሊስ ፈቅዷል። 

ፖሊስ በእነዚህ ቀናት “ስራውን የማይፈጽም ከሆነ፤ በፖሊስ ኃላፊነት የተጠርጣሪዎች መብት እንደሚጠበቅ” ችሎቱ ገልጿል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመጠባበቅ ለሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ መስከረም 11፤ 2015 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት የዛሬውን የችሎት ውሎ አጠናቅቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)