የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር “አራት ግቦች” እንዳሉት አሜሪካ ገለጸች

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግር መራዘም፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን እንደሚጠቁም የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ ተናገሩ። ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው የሰላም ንግግር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። 

ቃል አቃባዩ ይህን ያሉት፤ ስምንተኛ ቀኑን ስላስቆጠረው የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት የሰላም ንግግርን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ ነው። ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተጀመረው የሰላም ንግግር እስከ እሁድ ጥቅምት 20 እንደሚቆይ የደቡብ አፍሪካ መንግስት አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፤ ንግግሩ እስከ ትላንት ምሽት መቀጠሉን ከቦታው የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።

በፕሪቶሪያ ከተማ እየተካሄደ ለሚገኘው ለዚህ የሰላም ንግግር የተቀመጠ የቀን ገደብ እንደሌለ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ቃል አቃባይ ኤባ ካላንዶ ትላንት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል። በንግግሩ ላይ በ“ተሳታፊነት እና በታዛቢነት” እየተካፈሉ የሚገኙት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፤ ንግግሩ እስከሚያበቃበት ዕለት ድረስ በደቡብ አፍሪካ እንደሚቆዩ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።

የሰላም ንግግሩ እስከ ረቡዕ ድረስ ይቀጥላል መባሉ የሂደቱን አለመሳካት ያመልክት እንደሆነ የተጠየቁት ፕራይስ፤ ሁለቱ ወገኖች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን የሚጠቁም ነው ብለዋል። የሰላም ንግግሩ መራዘም ሁለቱ ወገኖች “አብረው ለመቀመጥ ፈቃደኛ ሆነው መቀጠላቸውንም አመላካች” ጭምር ሊሆን እንደሚችልም ጠቁመዋል። የደቡብ አፍሪካው ውይይት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና ህወሓት “ልዩነታቸውን የሚወያዩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ማጥበብ የሚቀጥሉበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም ሀገራቸው ከሰላም ንግግሩ የምትጠብቀውን አመልክተዋል። 

ፕራይስ በትላንቱ ዕለታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር አራት ግቦች እንዳሉት አስረድተዋል። አፋጣኝ የግጭት ማቆም ላይ መድረስ፣ ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማድረስ፣ የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ተጨማሪ እርምጃዎች መውሰድ እና የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ መውጣታቸውን ማረጋገጥ ፕራይስ የጠቀሷቸው የሰላም ንግግሩ አራት ዋነኛ ዓላማዎች ናቸው። በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የሚገኘው የሰላም ንግግር ሁለቱ ወገኖች ”ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ” እና ለአራቱ ግቦች ስኬት “መልካም ዕድል” እንደሆነ ቃል አቃባዩ ጠቅሰዋል። 

ከነገ በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 24፤ 2015 ሁለተኛ ዓመቱን በሚደፍነው የሰሜን ኢትዮጵያዊው ጦርነት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና ግፎች መፈጸማቸውን ያጋለጡ በርካታ ተአማኒ ሪፖርቶች መኖራቸውን በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያስታወሱት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቃባይ፤  የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት መጠበቅ አሁንም “አንገብጋቢው ጉዳይ” እንደሆነ ጠቅሰዋል። “በግጭቱ ወቅት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች እጅግ እንደሚያሳስቡን በድጋሚ እንገልጻለን” ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ ሁሉም ታጣቂ ኃይሎች መሰል ጥቃቶች አቁመው ለሰላማዊ መፍትሔ ዕድል እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በትላንቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ላይ በተሳተፉ ጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ያልተረጋገጡ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች” ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገራት እና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት መልሶ ለማጤን እንደሚገደድ ማስታወቁን የተመለከተ ይገኝበታል። የኢትዮጵያ መንግስት ላቀረበው ውንጀላ ያቀረበውን “መረጃ” እና “ዓላማውን” መመልከት እንደሚኖርባቸው የገለጹት ኔድ ፕራይስ፤ “የዩናይትድ ስቴትስ ዓላማ፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሔደው የሰላም ንግግር ግብ ቀላል ነው። ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ የለውም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በደቡብ አፍሪካ እየተካሔደ ያለውን የሰላም ንግግር በተመለከተ በሳምንቱ መጨረሻ ከቻይናው ሲቲጂኤን የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ቃለ መጠየቅ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ “ከግራ እና ከቀኝ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች” የሰላም ንግግሩን “ከባድ” ሊያደርጉ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር። “ህወሓት የአገሪቱን ህግ እና ህገ መንግስቱን እንዲያከብር ለማሳመን እየሞከርን ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጥቅማችንን ተረድተው፤ በህገ መንግስታቸው አምነው በዚሁ መሰረት ቢሰሩ ኖሮ ሰላም ይፈጠር ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)