በአማኑኤል ይልቃል
አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ አቶ ተስፋዬ ይገዙን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ። ምክር ቤቱ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግስት ዋና ተጠሪ እንዲሆኑ የተመደቡትን የአቶ አለማየሁ ባውዲ ሹመትንም አጽድቋል።
ከትላንት ነሐሴ 12፤ 2015 ጀምሮ በአርባ ምንጭ ከተማ መስራች ጉባኤውን እያካሄደ ያለው የደቡብ ኢትዮጵያ ምክር ቤት፤ በዛሬው ውሎው ከተመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ የቀረቡለትን የመንግስት ኃላፊዎችን ሹመት ማጽድቅ ነበር። በዚሁ ጉባኤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ጥላሁን ከበደ፤ የስድስት ኃላፊዎችን ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በቅድሚያ ያቀረቡት፤ ለክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ያጯቸውን አቶ ተስፋዬ ይገዙን ነው። በደቡብ ክልል ተመሳሳይ የስልጣን ደረጃ የነበራቸው አቶ ተስፋዬ፤ የከተማ እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊነትንም ደርበው ሲሰሩ ቆይተዋል። አቶ ተስፋዬ በደቡብ ክልል ውስጥ በቆዩባቸው ዓመታት፤ የወጣቶች እና ስፖርት፣ የግብይት እና ህብረት ስራ እንዲሁም የውሃ እና ማዕድን ቢሮዎችን በኃላፊነት መርተዋል።
በክልል ከነበራቸው የኃላፊነት ቦታ የወላይታ ዞንን እንዲስተዳድሩ በአንድ ወቅት ተመድበው የነበሩት አቶ ተስፋዬ፤ ወደ ፌደራል በመዘዋወርም ሰርተዋል። አቶ ተስፋዬ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን፤ በወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነበሩ። የፌደራል መንግስት የቤቶች ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተርም ሆነው አገልግለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የመልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የሰሩት አቶ ተስፋዬ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመራጭም ነበሩ። አዲሱ ተሿሚ በፓርላማ አባልነት ዘመናቸው፤ የተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ዋና ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ሰርተዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ ሁሉ በዛሬው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ውሎ ሹመታቸው በሙሉ ድምጽ የጸደቀላቸው ሌላኛው ኃላፊ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ አለማየሁ ባውዲ ናቸው። አቶ አለማየሁ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ዋና ተጠሪ ሆነው በዛሬው ጉባኤ ሲሾሙ፤ አቶ ዮሃንስ በየነ እና አቶ ዳዊት ገበየ ደግሞ ምክትል የመንግስት ዋና ተጠሪ ሆነዋል።
አዲሱ የክልሉ የመንግስት ተጠሪ፤ የመንግስት ኃላፊነት ስራቸውን የጀመሩት በደቡብ ኦሞ ዞን ነው። የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው የሰሩት አቶ አለማየሁ፤ ወደ ደቡብ ክልል ከተዛወሩ በኋላ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። አቶ አለማየሁ ከመስከረም 2014 ጀምሮ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የመልካም አስተዳደር ክላስተር አስተባባሪም ነበሩ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በዛሬው ጉባኤው፤ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ በኃላፊነት የቀረቡትን ዶ/ር አበባየሁ ታደሰን እና የውሃ፣ ማዕድን እና ኢነርጂ ቢሮን በኃላፊነት እንዲመሩ የተመረጡትን የአቶ አክሊሉ አዳኝን ሹመትም አጽድቋል። ክልሉ የሌሎች ቢሮ ኃላፊዎችን መልምሎ በዛሬው ጉባኤ ላይ በዕጩነት ማቅረብ ያልቻለው፤ “ለምስረታ ጉባኤ በርካታ ስራዎች በመደራረባቸው” ምክንያት መሆኑን ዛሬ የተሾሙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታውቀዋል።
“ክፍተት እንዳይፈጠር እና ስራ እንዲቀጥል” ሲባል፤ በብልጽግና ፓርቲ እና በአስተዳደር ምክር ቤቱ የሚመረጡ ኃላፊዎች ሹመታቸው እስከሚጸድቅ ድረስ በስራ ላይ እንዲሰማሩ፤ የክልሉ ምክር ቤት እንዲፈቅድ አቶ ጥላሁን ጥያቄ አቅርበዋል። ምክር ቤቱ ሌላ ጉባኤ ጠርቶ ተሿሚዎችን እስከሚያጸድቅ ድረስም፤ የአስተዳደር ምክር ቤቱ “በውክልና” ኃላፊነቱን እንዲወስድም ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪነት ጠይቀዋል። ይህ የርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄ የቀረበለት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ ሀሳቡን በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)