ላለፉት ስድስት ዓመታት አዲስ አበባን የመሩት አዳነች አቤቤ፤ የከተማይቱ ከንቲባ ሆነው በድጋሚ ተመረጡ። ከንቲባ አዳነችን “በሙሉ ድምጽ” የመረጠው፤ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 20፤ 2019 መስራች ጉባኤውን ያደረገው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ነው።
የከተማይቱ ምክር ቤት ካሉት 158 መቀመጫዎች መካከል 134ቱ የተያዙት በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው። ባለፈው ግንቦት ወር በተደረገው ምርጫ፤ ገዢው ፓርቲ ያልተወዳደረባቸውን 24 የምክር ቤት መቀመጫዎች 12 የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪ ተከፋፍለዋቸዋል።
ከእነዚህ አዳዲስ የተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮች ተቃውሞም ሆነ ድምጸ ተዐቅቦ ያልገጠማቸው ከንቲባ አዳነች፤ በአዲስ አበባ ከተማ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ መለስ አማካኝነት ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። አዳነች ለቦታው በድጋሚ ከመመረጣቸው አስቀድሞ የትምህርት ዝግጅታቸው እና የስራ ልምዳቸው፤ በትላንትናው ዕለት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው በተሾሙት ዶ/ር ጀማሉ ጀንበር ቀርቧል።

“አዳነች አቤቤ በመሩበት ቦታ ሁሉ በወጤታማነት ሌብነትን እና ሙስናን በመጸየፍ እና በመዋጋት የሚታወቁ፣ ተጨባጭ ለውጥ ያስመዘገቡ፣ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሪ ናቸው” ሲሉ ዶ/ር ጀማሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ከንቲባዋ “ሁሉንም ዜጋ በእኩል አይን በማየት፣ አብሮነትን በመገንባት እና ሀገራዊ ራዕይን በማራመድ የሚታወቁ [ናቸው]” ሲሉም አሞግሰዋቸዋል።
ከንቲባዋ “በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ የማይናወጡ፣ ጽናት ያላቸው፣ መፍትሔ አፍላቂ” መሆናቸውን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት የገለጹት ዶ/ር ጀማሉ፤ አዳነች “የከተማ አስተዳደሩ አመራር ለህዝብ ከማይጠቅሙ ደባል አጀንዳዎች እና መሳሳቦች ወጥቶ…የጋራ ዓላማ እና አንድነት ፈጥሮ እንዲንቀሳቀስ አስችለዋል” ሲሉም አክለዋል።
የገዢው ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ ብልጽግና ፓርቲ አዳነችን ለአዲስ አበባ ከንቲባነት በድጋሚ በዕጩነት ያቀረበበትን ምክንያትም አስረድተዋል። አዳነች በከንቲባነታቸው ዘመን “ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሰርተው እና በአርአያነት መርተው” “ተጨባጭ ለውጥ እና ውጤት ያስመዘገቡ” መሆናቸው ለዕጩነት እንዳበቃቸው ዶ/ር ጀማሉ አስረድተዋል።

ያለ ምንም ተቀናቃኝ በዕጩነት ቀርበው የተመረጡት ከንቲባ አዳነች፤ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ ለከተማይቱ ነዋሪ ንግግር እንዲያደርጉ በአፈ ጉባኤዋ ተጋብዘዋል። አዳነች 14 ደቂቃ በወሰደው ንግግራቸው፤ በቅድሚያነት ያነሱት የሰባተኛውን ዙር ምርጫ ውጤት ነው።
በዚህ ምርጫ ለገዢው ብልጽግና ፓርቲ ድምጽ የሰጠው መራጭ ቁጥር “ከፍተኛ” መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ “የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን የመረጡ ዜጎች ድምጽ ተደምሮ ሲታይ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም” ብለዋል። “የመረጠንም ሆነ ያልመረጠን የአዲስ አበባ ነዋሪ እኩል መብት ያለው ነዋሪ ነው። እኩል ክብር ይገባዋል። እኩል አገልግሎትም የማግኘት መብት አለው” ሲሉም ተደምጠዋል።
“ለመረጠንም ሆነ ላልመረጠን የከተማችን ነዋሪዎች በታማኝነትና በእኩልነት በክብር የማገልገል ግዴታችንን በሚገባ እንወጣለን” ሲሉ ቃል የገቡት ከንቲባ አዳነች፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት አስተዳደራቸው ሊያከናወን ያቀዳቸውን ጉዳዮች አብራርተዋል። አስተዳደራቸው በእነዚህ ዓመታት የሚሰራው ስራ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የዕለት ከዕለት ኑሮ “በተጨባጭ ማሻሻል የሚችል” እና “በዚህም የሚለካ” መሆን እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።
“ከእንግዲህ ልማታችንን የምንለካው በሰራነው ፕሮጀክት ብዛት ወይም በቁጥር በሚተነተን ሪፖርት አይሆንም”
“ከእንግዲህ ልማታችንን የምንለካው በሰራነው ፕሮጀክት ብዛት ወይም በቁጥር በሚተነተን ሪፖርት አይሆንም። ይልቁንም አንዲት እናት ምን ያህል የኑሮ ጫና ቀነሳላት? አንድ ወጣት ምን አይነት ኑሮውን የሚያሻሽል ጥራት ያለው የስራ እድል አገኘ? አንድ ነጋዴ የመንግስት አገልግሎት ሳይንገላታ በክብር አገኘ ወይ? አንድ ቤተሰብ ምን ያህል የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ ጥራት ያለው ትምህርት እና የጤና አገልግሎት፣ ውሃ፣ መንገድ፣ ትራንስፖርት አገኘ? ይሄም በኑሮ እና በአኗኗሩ ላይ ምን ለውጥ አመጣ? የስራችን የመጨረሻ ውጤት እነዚህን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ማድረግ መሆን ይገባዋል” ሲሉም ከንቲባ አዳነች አጽንኦት ሰጥተዋል።
አዳነች በዚሁ ንግግራቸው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲያከናውን የቆየውን የኮሪደር ልማት፤ በቀጣዩ ዓመታትም እንደሚቀጥል ፍንጭ ሰጥተዋል። አስተዳደራቸው በቀጣዩቹ አምስት ዓመታት “ጥራት ያለው ሰፊ መሰረተ ልማት” እንደሚገነባ የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ “ያረጁ እና የተጎሳቀሉ የአዲስ አበባ አካባቢዎችን እናድሳለን፤ መልሰን እንገነባለን” ሲሉም አክለዋል።
“የትናንቱ መልካም ስራችንን እናስቀጥላለን። ያጠፋነውን እናርማለን፣ ያጎደልነውንም እንሞላለን። ስኬታችንን እንጠብቃለን። ስህተታችን ከህዝብ አንደብቅም። ከስህተታችን ተምረን እንታረማለን” ሲሉም ከንቲባዋ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ባደረጉት ንግግር ማጠቃለያ ላይ ቃላቸውን ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

































