እስከ ዛሬ ድረስ አዲስ መንግስታቸውን በመሰረቱ ሁለት ክልሎች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ነባሮቹ መሪዎች ባሉበት እንዲቀጥሉ ሲደረግ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግን ላለፉት ሶስት ዓመታት ስልጣን ላይ የቆዩት ርዕሰ መስተዳድር ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል። በነገው ዕለት የደቡብ ኢትዮጵያን ክልል ጨምሮ ስድስት ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮቻቸውን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዛሬው ዕለት መሪዎቻቸውን የመረጡት የጋምቤላ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ናቸው። ሁለቱ ምክር ቤቶች የሰባተኛው የምርጫ ዘመን፤ የመጀመሪያ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት በጋምቤላ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ነው።
ባለፉት ዓመታት በጸጥታ መደፍረስ ሲቸገር የቆየው የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት፤ ነባሮቹን የክልሉን መሪዎች በያዙት ስልጣን እንዲቀጥሉ ይሁንታ ሰጥቷል። አዲስ አፈ ጉባኤ በመሾም ስራውን የጀመረው ምክር ቤቱ፤ ባለፉት ሁለት ዓመት የጋምቤላ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት የመሩትን አለሚቱ ኡሞድን በድጋሚ መርጧል።

ለስምንት ዓመታት በፌደራል የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት አለሚቱ፤ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነትን የተረከቡት በነሐሴ 2016 ዓ.ም በተደረገው የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ነበር። በዚሁ ጉባኤ ላይ የእርሳቸው ምክትል ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን፤ በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በኃላፊነት ቦታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ ረቡዕ መስከረም 20 የመንግስት ምስረታውን ያከናወነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ባሉበት እንዲቀጥሉ ቢያደርግም በምክትል ከንቲባ ላይ ለውጥ አድርጓል። ለስድስት ዓመታት በምክትል ከንቲባ ኃላፊነት ላይ የቆዩት አቶ ዣንጥራር አባይ፤ ባለፉት ዓመታት የደሴ ከተማን በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነት በመሩት አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ተተክተዋል።
አቶ ሳሙኤል ከምክትል ከንቲባነታቸው ባሻገር የከተማይቱን የፕላን ቢሮ በኃላፊነት ይመራሉ። እርሳቸውን ጨምሮ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባል በመሆን ሹመት የተሾሙ 14 አመራሮች፤ አዲስ መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል።
ከእነዚህ መካከል የከተማይቱን የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃይል ልማት ቢሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ በኃላፊነት እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ጥላሁን ከበደ ይገኙበታል። አቶ ጥላሁን ከህዝበ ውሳኔ በኋላ በነሐሴ 2015 በይፋ የተመሰረተውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ ለሶስት ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት ሲመሩ የቆዩ ናቸው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ከነገ መስከረም 21 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚያካሄደው መስራች ጉባኤው፤ እርሳቸውን የሚተካ አዲስ ርዕሰ መስተዳድር ይመርጣል። እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሁሉ በነገው ዕለት በየምክር ቤቶቻቸው መስራች ጉባኤ የሚያካሄዱት፤ አፋር፣ ሲዳማ፣ አማራ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮቻቸውን ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከትላንት በስቲያ መስራች ጉባኤውን ያደረገው ጨፌ ኦሮሚያ፤ ክልሉን ለሰባት ዓመታት የመሩትን አቶ ሽመልስ አብዲሳን በድጋሚ የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጎ መምረጡ ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በዚሁ ጉባኤው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትን አቶ አወሉ አብዲን ከኃላፊነታቸው በማንሳት በአቶ ከፍያለው ተፈራ መተካቱ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


































