በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት እና የሚያለሙበት ጊዜ አሁን ነው” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት እና የሚያለሙበት ጊዜ አሁን ነው” አሉ። ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ ዜጎች የአሁኑ ጊዜ “ወደ ውጭ የሚያስቡበት ሳይሆን ወደ ውስጥ የሚያስቡበት ነው” ሲሉም ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት አዲስ አበባ በሚገኘው የሳይንስ ሙዚየም ከትላንት ማክሰኞ መስከረም 29፤ 2016  አንስቶ መታየት የጀመረውን ሀገር አቀፍ የቱሪዝም እና ሆስፒታሊቲ አውደ ርዕይ በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ዘርፍ “የሚያስፈልጉ” እና “ጎልተው የሚታዩ” አምስት ዋና ዋና ነገሮችን “ከሚገባው በላይ” ያሟላች መሆኑን አብይ የጠቀሱት አብይ፤ ከእነርሱ መካከል አንዱ የ“ነባር ባህሎች” መገኛነት መሆኑን አመልክተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በልጆች አስተዳደግ ረገድ እያጋጠማቸው ነው ያሉትን ተግዳሮት፤ በኢትዮጵያ ካለው ባህል ጋር በማነጻጸር አንስተዋል። “የሰው ልጅ በባህሪው ራሱን መተካት፣ ትውልድ ማስቀጠል፤ በተፈጥሮ የተሰጠው ውስጣዊ ማንነት የሚፈልገው ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ “በሌላው ዓለም” ችግር እንደሚታይ ገልጸዋል። 

በውጭው ዓለም ያሉ የሚወለዱ ልጆች “ልጅነታቸውን አምነው፣ የተፈጥሮ ማንነታቸውን አምነው ማደግ አስቸጋሪ ሆኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወላጆቻቸው ተምረው፣ ዲግሪ ይዘው፣ ቤት እና መኪና መግዛት ቢችሉም ልጆቻቸውን ካጡ “ትርጉም የለሽ” እንደሆነ ጠቁመዋል። “ልጆችን ማትረፍ የሚቻለው በሀገር ባህል እና በሀገር ቅርስ ስለሆነ ለማሳሰብ ያህል ነው” ሲሉም ለችግሩ መፍትሔ ነው ያሉትን ጠቁመዋል። 

ወቅቱ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ዜጎች ስለ ሀገራቸው የሚያስቡበት መሆኑን በንግግራቸው ያነሱት አብይ፤ “አሁን ጊዜው ድህነትን የምንታገልበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ያላትን መልካም ነገር የምናወጣበት እና የምንሰበሰብበት ጊዜ ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)