ከሚኒስትርነታቸው የተነሱት ጫልቱ ሳኒ፤ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

ላለፉት አራት ገደማ ዓመታት የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስትር የነበሩት ጫልቱ ሳኒ፤ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ መስከረም 18፤ 2019 በሰጡት ሹመት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ጫልቱ፤ በቦታው ላይ ለዘጠኝ ዓመታት የቆዩትን ዶ/ር ረሻድ ከማልን ይተካሉ።

ዶ/ር ረሻድ ዛሬ በተካሄደው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መስራች ጉባኤ ላይ፤ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ከተሾሙ ስድስት ባለስልጣናት አንዱ ናቸው። ዶክተር ረሻድ ሲመሩት የነበረው እና ጫልቱ በዋና ስራ አስፈጻሚነት የሚረከቡት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፤ ከ50 ዓመታት ገደማ በፊት በመንግስት የተወረሱ ቤቶችን እንዲያስተዳድር በኤጀንሲ ደረጃ የተቋቋመ ነው።

ተቋሙን የመምራት ኃላፊነት የተረከቡት ጫልቱ፤ በሹመት ወደ ፌደራል መንግስት ከመዘዋወራቸው በፊት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነበሩ። ጫልቱ በስራ ላይ ከሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቢኔ፤ ወደ ሌላ የመንግስት መስሪያ ቤት የተዘዋወሩ ሁለተኛዋ ሚኒስትር ሆነዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ ባለፈው ሐሙስ መስከረም 14፤ 2019 የኢትዮጵያ ኒውክለር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል። ዶ/ር አብርሃም በኮሚሽኑ የተኩት፤ ወጣቱን የመንግስት ባለስልጣን አቶ ሳንዶካን ደበበን ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)